
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን ለ1446ኛው የዒድ አል ፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1446ኛው የዒድ አል ፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ!
ዒድ አል ፈጥር ሕዝበ ሙስሊሙ ቅዱሱንና ታላቁን የረመዳን ወር ለሀገራችን ሰላምና ፀጋ፤ ለመላው ህዝባችን ፍቅርና አንድነት በፆምና ዱአ አሳልፎ ከፈጣሪ እዝነትና በረከት የሚቀበልበት ልዩ ቀን ነው፡፡
በእምነቱ አስተምህሮ ሰላም፤ ኅብረትና አንድነት በእስልምና ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ በዓሉን በታላቁ የረመዳን ወቅት ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን የኢፍጣር ማዕድ በአብሮነት እንደተቋደስን ሁሉ፤ ኅብረትና አንድነታችንን ይበልጥ አጎልብተን ለጋራ ቤታችን ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና አብሮ በመቆም ማክበር ይገባል፡፡
ይህ ወቅት እንደሀገር ከመቸውም ጊዜ በላይ ህብረታችን፤ መተባበራችን እና መደጋገፋችን አስፈላጊ የሆነበት እንደ መሆኑ፤ በዓሉን ስናከብር የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሰረት ሰላምና ወንድማማችነትን ይበልጥ በማጎልበት መሆን ይኖርበታል፡፡
በዓሉን ስናከብር ለዘመናት የገነባነውን የሰላም፤ የመቻቻል፣ የመደጋገፍ እና የአንድነት እሴቶች በማጠናከር እና በየተሰማራንበት ዘርፍ ሀገራችንን በሀቀኝነት በማገልገል የድርሻችንን እየተወጣን እንዲሆን አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።
ዒድ ሙባረክ!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር