የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለደመራ እና መስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፤ መስቀል የፍቅር ኃያልነት የተገለጠበት፤ የሰላምና የድኅነት አርማ በመሆኑ፤ በዓሉን የእምነቱ አስተምሮ በሚያዘው መሠረት ዕርቅና ይቅርታን በማውረድ እና ፍቅርንና መከባበርን በማስፈን ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ እንኳን ለደመራ እና መስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
መስቀል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ዘላለማዊ ሕይወት ዋጋ የከፈለበት፤ ቤዛ ዓለም የተከናወነበት መንበር በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ክብር የሚሰጠውና በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡
በዓሉ ምእመኑ በየአካባቢው በኅብረት ደመራ በመደመር አንድነታቸዉን በሚገልጹ፣ በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ኩነቶች በአደባባይ የሚከበር ልዩ በዓል ነወ፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሰው ልጆች ቅርስነት የተመዘገበ፤ ህዝቦችን ማስተሳሰር የቻለ ድንቅ ዕሴታችንና የሀገራችን ሀብት ነው፡፡
መስቀል የፍቅር፤ የአንድነትና የመተሳሰብ ተምሳሌት በመሆኑ፤ በዓሉን ስናከብር የመረዳዳትና የአብሮነት ዕሴታችንን በጠበቀ መልኩ በመጠያየቅ፤ በመተሳሰብ እና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል፡፡
ብርሃነ መስቀሉ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን፣ ከፈተና ወደ ድል መጓዝን ማብሰሪያ ምልክት ሲሆን፤ ደመራው ፈታኙን ወቅት የመሻገራችን ብስራት፤ የመጪው የብሩህ ተስፋ ስንቅ የህብረታችን ምልክት ነው፡፡
በዓሉን ስናከብር፤ ከመስቀሉ የፅናትና የብርሃን ተምሳሌትነት ትምህርት በመውሰድ፤ ለክልላዊና ሀገራዊ ራዕዮቻችን ስኬት፤ በየወቅቱ የሚገጥሙንን ጊዜያዊና ወቅታዊ ፈተናዎች በፅናት በማለፍ፤ ለቀጣይ ድል መብቃት እንደምንችል በማሰብ ሊሆን ይገባል።
መስቀል በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት፤ የፍቅር ኃያልነት የተገለጠበት፤ የሰላምና የድኅነት አርማ በመሆኑ፤ በዓሉን አስተምሮው በሚያዘው መሠረት ዕርቅና ይቅርታን በማውረድ እና ፍቅርንና መከባበርን በማስፈን ማክበር ይገባል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።
በድጋሚ መልካም የደመራ እና የመስቀል በዓል!!
ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ!