ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በተከሰተ የመሬት ናዳ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን፤ በካዎ ኮይሻ ወረዳ፤ በጤፓ ቀበሌ ዛሬ ረፋድ 5 ሠዓት አካባቢ በተከሰተ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡

በአካባቢው ካለው የዝናብ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ጥረት በመደረግ ላይም ይገኛል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዛሬ ረፋድ 5 ሠዓት ገደማ በወላይታ ዞን፤ በካዎ ኮይሻ ወረዳ፤ በጤፓ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው፤ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት፡-

 “ዛሬ በክልላችን በዎላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤምፖ ቀበሌ በተከሰተው ናዳ አደጋ ህይወታቸዉን ያጡ ወገኖች ነፍሳቸዉ በአፀደ ገነት ከደጋጎች አጠገብ ፈጣሪ ያሳርፍ፤ ለመላዉ ቤተሰብ መጽናናትን ተመኘሁ።” ሲሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ “ፈጣሪ ይህንን አደጋ የመጨረሻ ያድርግልን” ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ተመኝተዋል፡፡

በድንገተኛ አደጋው ምክንያት በጠፋው የውድ ወገኖች ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ከሚገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

በየደረጃው ያለው አመራርና ባለድርሻ አካለትም ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከማሳወቅ በተጨማሪ ህዝቡን በማስተባበር የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡    

Leave a Reply