በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ቀበሌ በዛሬው ዕለት በአከባቢው ከጣለው ከፍተኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ በደረሰ የመሬት ናዳ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዛሬ ረፋድ አራት ሠዓት ገደማ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
“ዛሬ ሐምሌ 15/2016 ዓ/ም በክልላችን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ በተፈጠረዉ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የውድ ወገኖቻችንን ህይወት አጥተናል። እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ክስተት ነው።
በዚህ አደጋ ምክንያት ህይወታቸዉን ያጡ ወገኖቻችን ነፍሳቸዉ በአፀደ ገነት ፈጣሪ ያኑሪልን። ለቀሪ ቤተሰቦቻቸው መፅናናትንም እመኛለሁ።
በቀጣይ የተጎዱትን እና የተፈናቀሉትን የመደገፍ እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት አስፈላጊዉ ጥንቃቄ ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ እናደርጋለን”።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የክልሉ መንግስት በቀጣይ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑም ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድርግ የተቀናጀ ርብርብ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡