የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ክልሉ በህዝቦች ይሁንታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመሰረተ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የክልሉ መንግስት በሁሉም መስክ ውጤታማ ስራዎች መስራት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር ይበልጥ የሚያጎለብቱና ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይን ባጠረ ጊዜ ለማሳካት መሰረት የጣሉ ስኬቶች መመዘገባቸውን ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት መነሾ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ሰፊ ውይይት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
በዛሬው የምክር ቤቱ ሁለተኛ ቀን ውሎ ርዕሰ መስተዳድሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፡-
ክልሉ በሕዝቦች ፍቃድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በጋራ ተመስርቶ ወደ ስራ ሲገባ የክልሉ መንግስት ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳው በማድረግ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ በትኩረት መስራቱን ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው “ሰላምን በሰላሙ ጊዜ መስራት” አለብን ብለን በማቀድ የፀጥታ መዋቅሩን ለማጠናከር የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውንና በክልሉ እሰከታችኛው መዋቅር የዘለቀ የፀጥታ ምክር ቤት በማቋቋም የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በተደራጀ አግባብ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም በላይ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት ያላደረገ ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤት አያመጣም ብለን በማመን ከህዝባችን ጋር በመመካከርና ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ተቀራርበን የሰራን ሲሆን፤ ይህም በክልላችን አንጻራዊ ሰላም ለማረጋገጥ አስችሎናል ብለዋል፡፡
በተለይ የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችን የማጠናከር ስራዎችን በመስራትና የተለያዩ ፎረሞች በማዘጋጀት ከሀገር ሽማግሌዎች፤ ከሀይማኖት አባቶች፤ ከምሁራንና ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር በክልላችን የሰላምና ልማት ጉዳይ በጋራ በመምከርና አብሮ በመስራት ክልሉን የሰላም ተምሳሌት የማድረግ ትልማችንን ዕውን ለማድረግ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ህዝቦች ነባር ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶችና የሰላም ግንባታ ተቋማት ባለቤት መሆናቸውን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሰት እኚህን በክልሉ ያሉ ማህበራዊ ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማጽናት በቀጣይም የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከአጎራባች ዞኖችና ክልሎች ጋር በቀጠናዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጠንካራ የስራ ግንኙነት በመፍጠር የጋራ ጥረት በማድረግም ላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
ለቀጠናው ሰላምና ፀጥታ በዋናነት የህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ኮንተሮባንድ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ አመራሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በተቀናጀ አግባብ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምላሻቸው ከዳሰሱዋቸው ጉዳዮች መካከል ከመሰረተ ልማት እና ከተቋማት አገልግሎትና ተደራሽት ጋር የተያያዘ ይገኝበታል፡፡
የክልሉ መንግስት ከተቋማት አገልግሎት እና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ከፌዴራል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነት በክልሉ 712 የገጠር ቀበሌያት ብቻ የመብራት አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ገልፀዉ ከተደራሽነት አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂዎች ተደራሽነት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት የገጠሩን ማህበረሰብ የታዳሽ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከመሠረተ-ልማት አዉታሮች ጋር በተያያዘ ችግር እየፈጠረ ያለዉ ስርቆትን በመከላከል ረገድ የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀው የመሠረተ-ልማት አውታሮቻችንን የመንከበካብና የመጠበቅ ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ሚላሽ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ ደመወዝ መክፈል ግዴታ እንጂ በራሱ ስኬት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው የሚመደበው በጀት በቂ አለመሆኑን ገልጸው 75 በመቶ ወጪን የዉስጥ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለመሸፈን የተቀመጠዉን አቅጣጫ የጋራ ርብርብ በማድረግ ማሳካት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በየመዋቅሩ ለበጀት አስተዳደር ልዩ ትኩረት በመስጠት በጀትን በአግባቡ ለተመደበለት አላማ ማዋልና ወጪን በመቀነስ በቁጠባ መጠቀም የሚገባ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ 1 ሺህ 436 የተለያዩ ፕሮጀክቶች በዉሃ፣ ጤናና ሌሎች መሠረተ-ልማቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ይልቅ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከ UIDP የዓለም ባንክ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ክልሉ አዉቆ እንደሚሰራ ተድርጎ ፖለቲካ መንዛት ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው የዓለም ባንክ በራሱ ዕቅድ የሚመራ ተቋም በመሆኑ በፕሮጀክቶቹ አመራርና አካሄድ ላይ የክልሉ መንግስት ሚና እንደሌለው በግልጽ አስረድተዋል።
በቀጣይም በሚከናወኑ የከተማ ልማት ስራዎች መተማመኛዉ የከተሞች የዉስጥ ገቢ እና የመንግስት የበጀት ድጎማ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ለማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ በመስጠትና የከተማውን ኅብረተሰብ በልማቱ በማሳተፍ መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል።