ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በክልሉ አርባ ምንጭ ማዕከል የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ክልላዊ የክረምት በጎ ፍቃድ መርሃ ግብሩን በአርባ ምንጭ ከተማ በተለምዶ 03 ቀበሌ በመገኘት ያስጀመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ እርስ በርስ ከተባበርን፤ ከተጋገዝንና ከተደመርን ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመሻገር በጥረታችን ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ወጣቶች ክረምቱን ከአልባሌ ተግባራት ተቆጥበው የተለያዩ በጎ ተግባራትን በማከናወን ሊያሳልፉ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በጎ በመስራት ቃልችንን በተግባር ልንቀይር ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል።
ያሉን የተፍጥሮ ፀጋዎች ላይ በጎነትንና ቅንነትን በማከል ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቤታችን ትርፍ የሆኑ ነገሮች ለሌሎች በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ያለንን በማካፈል በጎነትን ባህል ልናደርግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ዛሬ እንደ ክልል የአንዲት አቅመ ደካማ ቤት በማደስ የጀመርነውን በጎ ተግባር በዘመቻ መልክ በመሳተፍ ወደ ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ክልሉ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ወጣቶችን ጨምሮ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከ 3 ሚሉዮን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ ውጤታማ ሰው ተኮር ተግባራትን ለማከናወን አቅዷል።
ለዚህም ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብሮች በሁሉም የክልሉ ማዕከላት የሚከናወኑ ይሆናል።
ከዚህ ቀደም በወላይታ ሶዶ፣ ዲላ እና በሳውላ የክልሉ ማዕከላት መካሄዱም ይታወሳል።