የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በጉባኤው የተገኙት ርዕሰ መስትዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም የተመለከተ ሰፋ ያለ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስትዳድሩ በሪፖርታቸው ክልሉ በዴሞክራሲያዊና እጅግ ሰላማዊ በሆነ ሂደት በህዝብ ይሁንታ በተመሰረተ ማግስት የክልሉ መንግስት የሽግግር ጊዜና የመደበኛ የልማት ስራዎች ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው በበጀት አመቱ በሁሉም አውታሮች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ክልሉን በስድስት ማዕከላት አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት በሁሉም አውታሮች፡- በህግ አውጪ፣ በህግ አስፈፃሚ እና በህገ ተርጓሚ አመርቂ ስራዎችን በመስራት የክልሉን የሽግግር ጊዜ በስኬት አጠናቆ ወደ መደበኛ የልማት ስራዎች በፍጥነት መሸጋገር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በበጀት አመቱ የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሁሉም የልማት መስኮች አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አያይዘው በክልሉ ህዝቦች የጋራ የመልማት ፍላጎት ላይ ማነቆ ሆኖ የቆየን ስር የሰደደ የነጠላ ትርክት እሳቤን ቀይሮ ገዥ የወል ትርክቶችን በማጽናት ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብዝኅነት ተምሳሌት በማድረጉ ረገድ ስኬት መመዝገቡንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በዋና ዋና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በተለይም በግብርና፤ ትምህርትና ጤና፤ ኢንቨስትመንት፤ መሰረተ ልማት፤ ስራ ዕድል ፈጠራ፤ ገቢና የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ዙሪያ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ እና መልካም አስተዳደር በበጀት አመቱ በተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በትኩረት ከዳሰሷቸው ዘርፎች አንዱ የግብርና ልማት ዘርፍ ሲሆን በበጀት አመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ለበልግ እርሻ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከዕቅድ በላይ በተሰሩ የበልግ ወቅት ስራዎች ከ753 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ60.3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት አመቱ ግብርናን በማዘመን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ለመስኖ ልማትና ለሜካናይዜሽን እርሻ ትኩረት ሰጥቶ መሰራቱንና አርሶ አደሩ ያለን የውሃ ሀብት ተጠቅሞ በአመት ሦሥቴ እንዲያመርት በማስቻል አበረታች ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም 132 ሺ ሄ/ር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ከ27.4 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ከተለያዩ አዝርት ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ በምርት ዘመኑ በሁሉም ሰብሎች በኩታ ገጠም እርሻ ከ186 ሺህ ሄ/ር በላይ በዘር መሸፈን መቻሉንም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በ2015/16 መኸር በአዝርዕትና በሆርቲካልቸር ዓመታዊና ቋሚ ሰብሎች ከ752 ሺህ ሄ/ር በላይ የእርሻ መሬት በዘር በመሸፈን ከ52 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት መሰብሰቡንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በ 8 ሺህ ሄ/ር በላይ ማሳ በማልማት አማካይ ምርታማነትን 28 ኩ/ል በሄክታር በማድረስ ከ247 ሺ ኩ/ል በላይ ምርት ለማግኘት መሰራቱን ገልፀዋል።
በክልሉ ለእንስሳት ሀብት ልማት ትኩረት በመስጠት በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ፤ ገበያ ለማረጋጋትና ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል አግባብ በትኩረት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በተለያዩ የእንስሳት ሀብት ልማት መስኮች 1 ሺህ 577 የሌማት ትሩፋት መንደሮችን ማደራጀት መቻሉም ታውቋል።
ከዚህ ውጪ በምርት ዘመኑ በቡናና ሻይ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውሉ የቅባት አዝርቶች የተሻለ ምርታማነት መመዝገቡም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ከሰላምና ፀጥታ አንጻር በክልሉ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ፤ የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር፤ የፀጥታ ምክር ቤትና የኃይማኖት ተቋማት ፎረም በማቋቋም እንዲሁም ነባር ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶችን፤ የሰላም ግንባታ ተቋማትንና ማህበራዊ የሰላም ዕሴቶችን በመጠቀም በተሰሩ በተደራጀ አግባብ በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች በክልሉ አስተማማኝ ሠላምና ፀጥታን ማረጋገጥ መቻሉም ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ለማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይ ለትምህርት እና ጤና ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች መስራቱንና አበረታች ውጤት ማግኘት መቻሉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በጤናው ዘርፍ በተለይ በጤና ተቋማት ግንባታና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም በቤተሰብ ዕቅድ እና ህብረተሰብ ጤና በርካታ ስራዎች ተሰርተው አበረታች ውጤት መመዝገቡ በርፖርቱ ተዳሷል።
በትምህርት ዘርፍ በበጀት አመቱ በሁሉም ዕርከኖች የትምህርት ተደራሽነት፤ ፍትሀዊነት እና ጥራት የማስጠበቅ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ለቀጣይ መሰረት የጣሉ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ያጋጠመን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ ርብርብ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡
በተለይ በርዕሰ መስተዳድሩ ሀሳብ አፍላቂነት በትምህረት በቶች ያጋጠመን የመጻህፍት ዕጥረት ለመቅረፍ በተጀመረው የ”አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” የሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ ከ213 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በ2017 በጀት አመት በማጠናከር መጻህፍትንና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶችን ተደራሽ ለማድረግ እነደሚሰራም ተገልጿል።
ወጣቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል በማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሁሉን አቀፍ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በበጀት አመቱ መሰራም ተገልጿል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍ በበጀት አመቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች በጥቅሉ ከ4.7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 157 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ከ45 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውም ተጠቁሟል፡፡
በክልሉ በሁሉም ዞኖች በተሰራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፕሮፋይሊንግ በክልሉ በአጠቃላይ ከ38 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1,581 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው በማልማት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የክልሉን ገቢ ከማሳደግ አኳያ በበጀት አመቱ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል፡፡
ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ የስራ እድል ፈጠራ ተግባራትን ማገዝ የሚያስችል የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት በማቋቋም ጭምር የተሰራ ሲሆን በበጀት አመቱ በከተማና በገጠር ስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች በርካታ ተግባራት መከናወኑን ተጠቅሷል፡፡
በዚህም በበጀት አመቱ ከ250 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ21 ሺህ በላይ የሚሆኑት በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የስራ እድል የተፈጠራላቸው መሆኑም ተመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ በተፈጠሩ የስራ ዕድሎች የሴቶች ተሳትፎ 47 በመቶ መሆኑም ታውቋል፡፡
የከተማ ልማት ስራዎችን በተደራጀ የህዝብ አቅም ለመፈጸም የህዝብ የልማት አደረጃጀትን በማሳተፍና በማነቃነቅ በርካታ የልማት ስራዎችን ማከናወን የተቻለ ሲሆን በገንዘብ ከ183 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ለልማት ማዋል መቻሉም ታውቋል፡፡
በተጨማሪ በበጀት አመቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በማቋቋሙ ረገድ ውጤታማ ስራ ከመሰራቱም በላይ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ወደ ስራ ማሰማራት መቻሉ በርፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን ሪፖርት በማድመጥ በሰጡት አሰተያየት የቀረበው ሪፖርት የክልሉን መንግስት የስራ አፈጻጸም የሚገልጽና አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውጭ የምክር ቤት አባላቱ በቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል፡-
የህገ-ወጥ ቅጥሮችና ዝዉዉሮች መበራከት፣ የዉጭ ሀገር የስራ ስምሪት ፍትሃዊነት ጉዳይ፤ ከ UIDP ፕሮግራም የተቀነሱ ከተሞች፣ ለመምህራን ጥራትና የተማሪዎች ምገባ የተሰጠው ትኩረት ፣ የመንገድና ዉሃ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችና የፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከላት የግብዓት ችግሮች፣ በቀድሞው ክልል እልባት ያላገኙ ተቋማት ንብረቶችና ሌሎች ጥያቄዎች በምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ርዕሰ መስተዳድሩ እና ሌሎች የአስፈፃሚ አካላት በነገዉ ዕለት ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።