ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “የህልም ጉልበት፣ ለእመርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝው መልዕክት በማስተላለፍ፤ ቀጣይ የስራ ስምሪት ሰጥተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በክልሉ በየደረጃው ያለው አመራር የክልሉ መንግስት የሰጠውን ከፍተኛ ኃላፊነትና ከህዝብ የተቀበለውን አደራ በአግባቡ በመወጣት፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለክልላዊና ሀገራዊ ህልምና ራዕዮቻችን ዕውን መሆን፤ አመራሩ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና በብቃትና በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ በስልጠናው ያገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለውጥ ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያሉ አስቻይ ሁኔታዎች፤ በተለይም በየአካባቢው ያለን ፀጋና እምቅ የመልማት አቅም እንዲሁም የህዝቡን ከፍተኛ የመልማት ፍላጎትና ተነሳሽነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ክልሉንና ሀገሪን ከተረጂነት ለማላቀቅ በቁጭት መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ፤ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር፤ የክልሉን ሰላም ማፅናት እና ዘላቂ ልማት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በትስስር በመስራት እና አቀናጅቶ በመምራት፤ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ከዳር ለማድረስ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አመራሩ በከፍተኛ የአገልጋይነት መንፈስ ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል፤ በተቋማት ዲጂታል አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ብልሹ አሰራርን በመዋጋት በየደረጃው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊቀርፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ወጪን መቀነስ፤ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፤ በግብርና ልማት ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር፤ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ማጠናከር፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፤ የትህምርትና የጤና ዘርፉን ማጠናከር፤ በከተሞች የካዳስተርና የኮርደር ልማት ስራዎች ማጠናከርና ማስፋት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ስኬት፤ የአመራሩ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የጋራ የሆነ ገዥ ትርክትን በመገንባት የታሪክ እምርታን ማምጣት እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት አቅጣጫ አመላክተዋል።