
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የበልግ የምርት ወቅትን አስመልክቶ ተገቢውን ትኩረት ለበልግ አዝመራ ስራዎች በመስጠት ላስቀመጥናቸው የምርት ዘመኑ ግቦች ስኬት መረባረብ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በክልላችን በ2016/17 የመኽር እርሻ ማስመዝገብ የቻልነውን አመርቂ ውጤት፤ በተያዘው የበልግ አዝመራ በመድገም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የጀመርነውን ሽግግር ለማፅናት በሁሉም የክልሉ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ተገቢውን ትኩረት ለበልግ አዝመራ ስራዎች በመስጠት በትኩረት መስራት ይገባል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት በክልላችን በስፋት እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ እርጥበትን በአግባቡ ተጠቅሞ በምርት ዘመኑ ለበልግ አዝመራ ምርታማነት ያስቀመጥናቸው ግቦችን በማሳካት የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩና ባለሙያው ከመቸውም ጊዜ በላይ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በክልላችን ቀዳሚ የትኩረት መስክ የሆነው የግብርና ልማት ዘርፍ የምግብና ስርዕተ ምግብ ዋስትናና ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ በሁሉም መስክ ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ላለምነው የተሳካ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ዕውን መሆን መሠረት በመሆኑ በዘርፉ የጀመርናቸውን፡- የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የማሻሻል፤ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድ እንዲሁም የመስኖ ልማትና የኩታ ገጠም እርሻን የማስፋፋት ተግባራትን በተያዘው የምርት ዘመንም በማጠናከር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ የተጀመሩ የበልግ ስራዎችን ጨምሮ የሌማት ትሩፋት፤ የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት፤ የቡና፤ እንሰት፤ ፍራፍሬና ሌሎች ቋሚ ሰብሎች ልማት እና ሌሎችም ኢንሼቲቮች አመራሩና ባለሞያው በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ በመምራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሰሩ አሳስባለሁ፡፡
ለውጥ የታታሪነትና የማያቋርጥ ጥረት ውጤት ነው!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር