አመራሩ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነትና ከህዝብ የተቀበለውን አደራ በአግባቡ በመወጣት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን ማዕከል አድርጎ በተዘጋጀው፤ ክልል አቀፍ የቀጣይ 90 ቀናት የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ ላይ ያተኮረ የአመራር የዉይይት መድረክ ተገኝተው መልዕክት ማስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፡- አመራሩ በጉባኤው የተቀበለውን ታላቅ የህዝብ አደራና የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጉባኤውን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች በአግባቡ በመተግበር የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የብልፅግና ራዕዮቻችን ዕውን መሆን አመራሩ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና በብቃትና በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ ነባራዊ ሁኔታን፤ አቅምን እና ያሉ አስቻይ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ዕቅድን ከልሶ በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ በመምራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ በቀጣይ ዘጠና ቀናት ሰው ተኮር ተግባራትን በማጠናከር ሰብዓዊ ልዕልናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር በቁጭት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

አመራሩ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።   

ፓርቲዉን በአሠራርና አደረጃጀት ማጠናከር፤ የክልሉን ሰላም ማፅናት፤ ወጪን መቀነስና የውስጥ ገቢን ማሳደግ፤ ምርታማነትን ማላቅ፤ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ማጠናከር፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፤ የኮርደር ልማት ስራዎች ማጠናከርና ማስፋት የቀጣይ ዘጠና ቀናት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የዘጠና ቀን ዕቅዱን ውጤታማ በሆነ አግባብ ተግባራዊ ለማድረግ አመራሩ በቀጣይ ሶስት ወር ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ተግባራትን በመምራት፤ በመከታተልና በመደገፍ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ዕውን ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ዋነኛ ተግባሩ ሊያደርግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በቀሪ ወራት የክልሉን ሕዝቦች ክልላዊ አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በተጠናከረ አግባብ የማከናወን እና የክልሉን ሰላም የማፅናት ተግባር ትኩረት የሚያሻው መሆኑንም በአጽንኦት ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አመራሩ በከፍተኛ የአገልጋይነት መንፈስ ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል፤ በተቋማት ብልሹ አሰራሮችን በጠንካራ ተቋማዊ አሰራር በመዋጋት እንዲሁም የዲጂታል አሰራርን ተደራሽ በማድረግ በየደረጃው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊቀርፍ እንደሚገባ አስምረዋል፡፡ 

በየዘርፉ በተቀመጡ ዕቅዶች ላይ እምርታዊ ዉጤት በማስመዝገብ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የአመራሩ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፡-

በአጠቃላይ ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላም፤ የልማትና የብልፅግና ህልም ስኬት እና ለህዝባችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አመራሩ ከተሰጠው በላይ በመስራትና ከሚጠበቅበት በላይ በመፈፀም ኢትዮጵያን በአለም ተወዳዳሪ ለማድረግ መረባረብ ይገባዋል ብለዋል፡፡

Leave a Reply