“አዲስ ዕሳቤ ፣ በአዲስ ክልል ወደ አዲስ ምዕራፍ” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት አጠቃላይ የክልል አመራር መድረክ በዎላይታ ሶዶ ተካሄደ

(ዎላይታ ሶዶ፣ መስከረም 24/2016 ዓም )በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ የታሪክ ተወዳሽ እንዲንሆን ያለንን የተፈጥሮ ፀጋ ካለን ውስን ሀብት ጋር በማጣመር የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ተግተን መስራት ይኖርብናል አሉ።

በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ክልሉን እንድንመራ እድሉ የተሰጠን አመራሮች ሳንሰራ እድሉ እንዳይመክንብን ዛሬ በእጃችን ባለ እድል የተሻለ ልማት ለማስመዝገብ ቀንም ማታም መስራት አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አቅምን በውጤት ችግርን በስኬት ለመግለጥ መሰጠት ይኖርብናል ሲሉ አስታውቀዋል።

ፈተናዎቻችንን ባማረ ውጤት ለመቀየር አመራሩ መፈጠንም መፍጠርም ይኖርበታል ያሉት ክቡር አቶ ጥላሁን ለውድቀታችን ምክንያት መደርደርን ክልሉ የማያስተናግድ መሆኑን በማወቅ አመራሩ በሙሉ ሃይሉ እና አቅሙ መረባረብ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

ብዙ ስራ ብዙ ጥያቄ ብዙ የህዝብ ፍላጎት ይጠብቀናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጊዜ የለኝም በሚል አስተሳሰብ ስራ ለነገ ማሳደርን በማስወገድ መፍጠን ይኖርብናል ሲሉ ጠቅሰዋል።

ወሬን ጊዜ ከልክለን ሙሉ ጊዜያችንን ተግባራችን ላይ በማዋል ቃላችን በተግባር ይገለጥ ዘንድ ይገባል ያሉት ክቡር አቶ ጥላሁን ፍጥነታችንን ከሚያደናቅፉ ከታሪ ኃይላትም መጠንቀቅ ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት የአመራር መሰጠትና የአቋም ጽናት ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ መመስተዳድሩ ለመተጋገዝና ለመረዳዳት በራችንን ክፊት በማድረግ ተግባቢ መሆን ያስፈልጋል ሲሉም አብራርተዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር፣ ህዝቡ የሰላሙ ባለበት እና የልማቱ ግንባር ቀደም ተወናይ እንዲሆን በትኩረት መሰራት ይጠበቅብናል ሲሉ ያብራሩት ክቡር አቶ ጥላሁን ለህዝቡም የምንሰጠው አገልገሎት ፈጣንና እርካታን የምሰጥ መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

ወጪ ቆጣቢ አሰራር በመከተል ፣ ገቢ አሟጠን በመሰብሰብ ፣ የተሻለ የስራ እድል በመፍጠር ውጤት ማስመዝገብ የግድ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የሴቶችንና የወጣቶችን ጠንካራ ተሳትፎ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል።

የግብርና ዘርፍ ልማቱን በትኩረት መምራት በእጅጉ ይፈለጋል። በትምህርት ዘርፉ የገጠመንን ስብራት በመጠገን ፣ በወረርሽኝ የሚታገለውን የጤና ዘርፍም የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት መረባረብ ይኖርብናል ሲሉም አክለው አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ ክቡር አቶ አለማየሁ ባዉዲ ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪዎች፣ የካቢኔ አባላትን ጨምሮ አጠቃላይ የክልሉ አመራር ተገኝተዋል።

Leave a Reply