በኢትዮጲያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ምርትን 85 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቀል፡፡
የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል መንግስት በክልሉ ፈጣን ዕድገት በማስመዘገብ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ከዳረገባቸው የልማት ዘርፎች አንዱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው በክልሉ ያለን የመልማት ፀጋ በመለየትና አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ክልሉ ያለውን አቅም በመጠቀም እና የግል ዘርፉን በስፋት በማሳተፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን በክልሉ ለማሳደግና ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ምርትን በአገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ እና ገበያን በማረጋጋቱ ረገድ ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በክልሉ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የግብዓት ምርት ልማት ትስስርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለወጪና ተኪ ምርቶች ዕኩል ትኩረት በመስጠት በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ የኢንዱስትሪ ተቋማትን በክላስተር በማቋቋም ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከርና ማስፋፋት የክልሉ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ሀብት ያፈሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን በኢንዱስትሪው ዘርፍ በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ርዕሰ መስትዳድሩ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በዘርፉ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስትዳድሩ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመው በክልሉ ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡