ከደረሰብን ልብ ሰባሪ ሐዘን በመውጣት በአስከፊ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም መረባረብ አለብን -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ   

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዚዲ ቀበሌ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የታወጀው ብሔራዊ ሐዘን ቀን ማጠቃለያ ሻማ የማብራት ስነ-ስርዓት በሳውላ ከተማ ተካሂዷል፡፡  

በክልሉ ጎፋ ዞን የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ላለፈ ወገኖቻችን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን ቀን ማወጁ ይታወሳል።

የብሔራዊ የሐዘን ቀን ማጠቃለያን ምክንያት በማድረግ በድንገተኛው አደጋ ውድ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን መታሰቢያ ሻማ የማብራት ስነ-ስርዓት በሳውላ ከተማ ተካሂዷል፡፡  

በስነ-ስርዓቱ የተካፈሉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መርሃግብሩ በጎፋ ዞን በተከሰተው አስከፊ ድንገተኛ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን አስበን በመፅናናት ከሀዘን ለመውጣትና ሙሉ ትኩሬታችንን ከአደጋው የተረፉ ወገኖች በዘላቂነት ለማማቋቋም በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡    

የደረሰብን አደጋ አስከፊና እጅግ መሪሪ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ መሪሪ ሀዘን ብንጎዳም ከሀዘን ስሜት በመውጣት በአደጋው ጧሪ ያጡ አረጋዊያንን፤ ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናትንና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በመደገፍ፤ በመንከባከብና በቋሚነት ለማቋቋም በመረባረብ ድጋፍችንን ልናሳይ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡    

በአደጋው ወገኖቻችን ለሰው ሕይወት ብለው ሕይወታቸውን የገበሩበት አጋጣሚ ልብ ሰባሪ ቢሆንም የጥላቻን ግንብ አፍረሰን በፍቅር፤ በመቻቻልና በአንድነት አንዳችን ለአንዳችን ከልብ መተሳሰብና መደጋገፍ እንዳለብን ያስተማረም ጭምር  ነው ብለዋል።  

በቀጣይ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በትኩረት በመስራት በተለይ የጀመረነውን የተራራ ልማት ስራ በማስፋትና አጠናክረን በመቀጠል ተመሳሳይ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድመን መከላከል ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዝናብ መጠኑም ከወትሮ የመጨምር አዝማሚያ ያለው በመሆኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የሚደረገው የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የአደጋው ልብ ሰባሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋውን ተከትሎ መላ ኢትዮጲያዊያን፤ የፌዴራል መንግስት፤ ክልሎች፤ አጋር ተቋማትና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ ጭምር ያሳዩት ወገንተኝነት ያበረታንና ከአደጋው ለተረፉ ወገኖችም ተስፋን የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ክልሎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአከባቢው ማህበረሰብ፣ ተቋማት፤ የሀይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች እንዲሁም አለም አቀፍ መንግስታት በማድረግ ላይ ስላሉት ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከፊታችን በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንና በአካባቢው በተጋላጭነት በጥናት የተለዩ ዜጎችን ከአካባቢው በማስወጣት በዘላቂነት የማቋቋም ከባድ ስራ ይጠብቀናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የክልሉ መንግስት የአደጋው ሰለባ የሆኑ ወገኖችንና ተጋላጮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸው የተጀመሩ የሰብዓዊና የገንዘብ ድጋፎችን በማጠናከር ወገኖቻችንን ለማቋቋም በመረባረብ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ዳግም እንድታሳዩን አደራ እላለሁ ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡  

በጧፍ ማብራት መርሃ-ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምር የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የዞንና የወረዳ አመራሮች፤ የደበጎ አድራጎት ተቋማት መሪዎች፤ አርትስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች፤ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ መላው የከተማው ኑዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን መታሳቢያ ሻማ የማብራት እና የሂሊና ፀሎት መርሃ-ግብር በሁሉም የክልሉ ማዕከላት እና የተለያዩ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን፤ መላው የክልሉ ህዝብ ከጎፋ ወገኖቹ ጋር በመቆም ወገንተኝነቱን አሳይቷል፡፡  

Leave a Reply