ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበርን በማስመልከት በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል ህዳር 29/2017 ዓ/ም የሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በልዩ ድምቀት በአርባ ምንጭ ከተማ ለማክበር፤ ክልሉ በልዩ ትኩረት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመላው ሕዝቦች የጋራ ትግል ሁሉም ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት፤ በፍትሃዊነትና በነፃነት የመኖር መብት ያጎናጸፋቸው ሕገ-መንግስት ህዳር 29 መጽደቁን ተከትሎ መከበር የጀመረው በዓሉ፤ የህዝቦች የዕርስ በርስ ትስስርና የባህል ልውውጥ መድረክ ሆኖ የፌደራል ሥርዓታችንን በማጎልበት ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እውነተኛ የዲሞክራሲ ማሳያ በሆነው፤ በህዝቦች መፈቃቀድ በተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት እንዲከበር መመረጡ ትክክልኛ ዕይታ መሆኑንም በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ክብረ በዓሉ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር፣ ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማፅናት እና ገዢ ትርክቶችን በማስረፅ ወቅታዊ ፈተናዎችን ለመሻገር አቅም መፍጠር የሚያስችል ዕድል የሚፈጠር እንደሆነም ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መጥቷል ያሉ ሲሆን፤ በማህበራዊ መስተጋብሩ ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ አብሮነትን እና የህዝቦች ትስስርን የሚያጠናክር ስለመሆኑ አንስተዋል።
ክብረ በዓሉ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር እና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአካታች ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ ባለበት ወቅት የሚከበር መሆኑን ገልፀው፤ ክብረ በዓሉ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፌደራሊዝምን እሳቤና እሴቶች በመላበስ ለሀገራዊ መግባባት የሚመክሩበት እና የብሔራዊነት ትርክትን በማጽናት ሕብረብሔራዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተጀመሩ የግብርና እና የቱሪዝም ኢንሸቲቮች ትልቅ ሀገራዊ ስኬት መመዝገብ መቻሉን ገልፀው፤ በዓሉ የሀገራችንን ፀጋዎች በሚያስተዋውቅ እንዲሁም የክልሉን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ ለማክበር ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በብሔራዊ ደረጃ የብሄር ብሄረሶቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበሩ፤ የወል ትርክቶችን በማስረጽ ህዝቦች ለጋራ ሀገራዊ ህልምና ራዕይ ስኬት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያግዝ፤ ብሄራዊ አንድነትን የሚፈጥር ብሎም ሀገራዊ መነቃቃትንና ብሄራዊ ተነሳሽነትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡
በክልላችን የበዓሉ መከበር ፋይዳው በእጅጉ የጎላ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ስኬት የራሱ ሚና የሚኖረው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዓሉ ክልሉ ያሉትን ዕምቅ አቅሞች የሚያስተዋውቅበት፤ ስኬቱንም የሚያነሳበት እና ልምድ የሚቀስምበት እንደሚሆንም ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም ከተከበሩት ለየት ባለ እና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመጨረሻም 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለማክበር የብዝኅ ህዝቦች መዲና ወደ ሆነችው ውብቷ አርባ ምንጭ ለሚመጡ እንግዶች ከወዲሁ መልካሙን በመመኘት መግለጫቸውን አጠናቀዋል።