የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ ተመረቀ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

ግንባታው በመጋቢት 2007 ዓ.ም የተጀመረው ሆስፒታሉ በ25 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈ ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታል ነው፡፡

ሆስፒታሉ የሄሊኮፕተር አምቡላንስ አገልግሎት ጭምር እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ሲሆን በምርመራ ደረጃ ዘመኑ የደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎችን የያዙ የምርመራ ማሽኖችንም ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉ ታውቋል፡፡

በዚህ ረገድ ኦክሲጅን ከማምረት በተጨማሪ ኦክሲጂኑን በየክፍሉ የሚያዳርስ መስመር፣ ዲጂታል የኤክስሬይ ማሽኖች፣ ሲቲ ስካን፣ የኤም አር አይ እና ዘመናዊ የአልትራሳውንድ ማሽኖችም ተገጥመውለታል።

ይህም አግልግሎት ፈላጊዎች ከዚህ ቀደም እስከ አዲስ አበባ ለህክምና የሚያደርጓቸውን ጉዞዎችንና አላስፈላጊ መጉላላት ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የሆስፒታሉን መመረቅ ገልጸው፣ ይህ ሆስፒታል ሰፊ መጠነ ራዕይ ያላቸው የህክምና አገልግሎቶች ለመስጠት የተገነባ ነው ብለዋል።

ገና ብዙ ርምጃ መራመድ ቢጠበቅብንም በጤናው ዘርፍ በቂ የህክምና አገልግሎት ለዜጎቻችን ለማቅረብ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ለዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በማቅረብ ሥራ ለሚተጉ የጤና ባለሞያዎች ምስጋናችንን እናቀርባለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ጥበቃ ሥርዓታችንን ለማዘመን በምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት ቀጣይ አስተዋፅዖችሁ እና አገልግሎታችሁ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በምረቃው መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ዋና አፈ ገባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዞን አመራሮች፤ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ተጋባዥ እንግዶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply