የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጎፋ ዞን የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አወጀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን፣ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ላለፉ ዜጎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።

የውሳኔው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ በመሬት መንሸራተት በደረሰ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈውን ነዋሪዎች በማስመልከት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈ ውሳኔ፡-

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን በተለያየ መንገድ እየገለፀ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው የአገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እየተመኘ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ወስኗል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001ን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሀዘን ቀን የማወጅ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ /2/ መሠረት ምክር ቤቱ በሥራ ላይ በማይኖርበት ጊዜ የተፈጠረ ክስተት ከሆነ የብሔራዊ የሀዘን ቀንና ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ የሚውለበለብበትን ሁኔታ በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የሚወሰን መሆኑን ይደነግጋል።

በመሆኑም ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ለ3 ቀናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በማሰብ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ሆኖ እንዲታወጅና በእነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፤ በኢትዮጵያ መርከቦች፤ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል።

Leave a Reply