19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት፤ በአርባ ምንጭ ከተማ ከህዳር 25 እስከ ህዳር 29/2017 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል፡፡
የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው የበዓሉን ዝግጅት የገመገሙ ሲሆን፤ ክብረ በዓሉ የሚከበሩባቸው ቦታዎች ዝግጅትም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
አፈ ጉባኤው ለዚሁ የስራ ጉዳይ አርባ ምንጭ አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ዋና አፈ ጉባኤው በነበራቸው የስራ ቆይታ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በመከናወን ላይ የሚገኙ የቅደመ ዝግጅት ስራዎችን ገምግመዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት 19ኛው ክብረ በዓል፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ እንዲከበር ሲወሰን መነሻ ምክንያቶች ነበሩት ያሉት አፈ ጉባኤው፤ የክልሉ ህዝቦች ላነሱዋቸው በክልል የመደረጃት ሕገመንግስታዊ ጥያቄ፤ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሕገመንግስታዊ ምላሽ ያገኙበት ወቅት ዋናው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀዳሚው የብዝኅ ህዝቦች ክልል መሆኑ ሌላው መነሻ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 76 ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል 32 በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪ አርባ ምንጭ ከተማ በክልሉ በየጊዜው እያደጉ ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዷ መሆኗ እንዲሁም ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለባትና በህብር ህዝቦች ማዕከልነቷ መታወቋ ክብረ በዓሉን ለማስተናገድ ተመራጭ ያደረጋት መሆኑን አብራርተዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔርች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤው፤ ይህንኑ በዓል በድምቀት ለማክበር የሚያስችል በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየቱን አስረድተዋል።
በዓሉ በክልሉ መከበሩ የክልሉን እምቅ አቅም እና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤው፤ ክብረ በዓሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለዓለም ከፍ አድርገን የምናስተዋውቅበት ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኩላቸው በዓሉን ከዚህ ቀደም ከተከበሩ በዓላት በተሻለ እና ለሀገር ትምህርት በሚሆን መልኩ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ የመድረኩ ዓላማም በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀሪ ጊዜያት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ስራዎችን ለመለየትና በትኩረት ለማከናወን መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ ክልሉ በዓሉን በድምቀት ለማዘጋጀት እንዲቻል በዐቢይና ንዕሳን ኮሚቴዎች አማካኝነት ያከናወናቸው ስራዎች ሪፖርት የክልሉ የህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀረበው ሪፖርት መነሾ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ውይይቱን ተከትሎ ክብረ በዓሉ የሚከበሩባቸው ቦታዎች ዝግጅት የመስክ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን፤ የደቡብ ኢትዮጰያ ክልል 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በተሻለ መልኩ በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን መመልከታቸውን አፈ ጉባኤ ተሻገር አገኘው በጉብኝቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡
ክቡር አፈ ጉባኤው በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ለማስከበር፣ ብዝኃነት እንዲጠናከር፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ስር እንዲሰድና ጤናማ የፌዴራል ሥርዓት እንዲጎለብት የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ሲከበርም፤ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የዜጎችን ኅብረብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር አግባብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ያለፉት የበዓሉ አከባበሮች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የፈጠረላቸው መሆኑንም ጠቅሰው፤ በቀጣይ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማፅናት ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መከበር በጋራ እንዲቆሙ በሚያስችል መልኩ ማክበር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በዓሉን ለማክበር በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ በመከናወን ላይ ያሉ ዝግጅቶች ስኬታማ መሆናቸውን መመልከታቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤው፤ ክልሉ ብቃት ያለው ዝግጅት በማድረጉ ክብረ በዓሉ በተለየ በድምቀት ይከበራል የሚል ዕምነት ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚከበረው 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ ዘርፈ ብዙ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ክብረ በዓሉን በድምቀት ለማሰናዳት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰው፤ የክብረ በዓሉ በየዓመቱ መከበር የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር እና በማጎልበት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከፈ ያለ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አክለው በክልሉ አዘጋጅነት የሚከበረው የዘንድሮ በዓል፤ በይዘትም ሆነ በድምቀት ለየት ባለ ሁኔታ ክልሉን በሚመጥንና የክልሉን ገፅታ እንዲሁም የባህልና የቱሪዝም ፀጋዎች በሚያስተዋውቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ክብረ በዓሉ ቀዳሚ የብዝኅ ህዝቦች መገኛ በሆነው ክልሉ መከበሩ በዓሉን ለየት ከማድረጉም ባለፈ፤ ለክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ተናግረው፤ በተለይ የህዝቦች ትስስርንና አንድነትን በማጠናከር ከወዲሁ በሰላሙና በልማቱ ረገድ መነቃቃት እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የበዓሉ አስተናጋጅ በሆነችው አርባ ምንጭ ከተማ፤ የከተማው ህብረተሰብን በንቃት በማሳተፍ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ጨምሮ የከተማ ጽዳትና ውበት እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን በማከናወን ለከተማው ዕድገት ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡
በዓሉን ለማክበር ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንግዶች፤ የክልሉ አንዱ ማዕከል በሆነው በወላይታ ሶዶ ከተማ የአንድ ቀን ቆይታ የሚኖራቸው መሆኑንም ገልፀው፤ ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።