ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የ2017 በጀት በተመለከተ ከዞን አስተዳደር እርከን አመራሮች ጋር በአርባምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችና የመልማት ፍላጎቶች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ በ2017 በጀት ዓመት የበጀት ድልድል የክልሉን ድርሻ በእጅጉ በመቀነስ የዞኖችን ድርሻ ከፍ ለማድረግ በመስተዳድር ምክር ቤት ተገምግሞ በክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት መፅደቁን ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት የበጀት ክፍፍል ድርሻው ሰማንያ በመቶ (80%) ለዞኖች እና ሃያ በመቶ (20%) ለክልል ማዕከላት እንዲሆን መወሰኑን አስረድተዋል።
በዚህም የክልሉ መንግስት የዞን አስተዳድር እርከኖች የ2017 ዓ/ም በጀት 30,080,453,587.2 (ሰላሳ ብሊየን ሰማንያ ምሊየን አራት መቶ ሃምሳ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ሰማንያ ሰባት ብር ከሁለት ሳንቲም) እንዲመደብ ወስኗል፡፡
የበጀት ድልድሉ የኢፌድሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች ያስተላለፈው ቀመርን መሰረት በማድረግ በመስተዳድር ምክር ቤት ታይቶና ተገምግሞ በክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ በጸደቀው የሀብት ማከፋፈያ ቀመር መሰረት ያደረገ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው የበጀት አመቱ ሃምሳ ሰባት በመቶ (57%) በጀት በውስጥ ገቢ የሚሸፈን መሆኑንና የተቀረው አርባ ሶስት በመቶ (43%) በፌደራል መንግስት ድጎማ የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በበጀት አመቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የውስጥ ገቢን ማሳደግ፤ ወጪ ቅነሳ እና ለበጀት አጠቃቀም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ በመምራትና ገቢን በአግባቡ በመሰበሰብ በውስጥ አቅም የልማት ፕሮጀክቶችን ለመሸፈን የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የዞን አስተዳዳሮች በበጀት አመቱ ካለፈው በተለየ በጀተን ለታለመለት ዓላማ በማዋል እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያስነሱ የልማት ፕሮጀክቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ በማጠነቀቅ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች መመለስ የሚገባቸው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ህዝቡን የልማቱ ባለቤት በማድረግና ኅብረተሰቡን በንቃት የሚያሳትፉ የልማት ስራዎችን በመስራት ተጠቃሚ ለማድረግ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት አመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት በመስራት እና የውስጥ አቅምን በማጎልበት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡