የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡   

በጉባኤው ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም በተመለከተ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ላይ በማተኮር ሰፋ ያለ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት በማድረግ የተወያየ ሲሆን የምክር ቤት አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከማድመጥና ከመወያየት በተጨማሪ የክልሉ ምክር ቤት የ6ኛ ዙር 3ኛ አመት የ2ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤን እና የክልሉ ምክር ቤት የ2016 በጀት አመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም በ2017 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ ተጠናቋል።

የምክር ቤቱ 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ለሦሥት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በቆይታው የክልሉ የ2017 በጀት ረቂቅ የበጀት አዋጅን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

ምክር ቤቱ በክልሉ መንግስት የ2017 በጀት አመት ረቂቅ የበጀት ዕቅድ ላይ በመወያየት ረቂቅ በጀቱን ያፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply