የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት 37.6 ቢሊየን ብር አፀደቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ተወስኖ የቀረበለትን የክልሉን መንግስት የ2017 ረቂቅ በጀት አስመልክቶ በጥልቀት ተወያይቷል፡፡

ምክር ቤቱ በመስተዳድር ምክር ቤት የቀረበውን የክልሉን መንግስት የ2017 ረቂቅ በጀት 37 ቢሊየን 600 ሚሊዮን 566 ሺህ 988 ብር በመመርመር በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጀቱ ከዚህ ቀደም በነበረው ክልል ሲነሱ የነበሩ የህግና የኢ-ፍትሃዊነት ጥያቄዎች እንዳይደገሙ በማሰብ የበጀት ድልደላዉ አሳታፊ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ህገ-መንግስቱ በሚያዘዉ መሠረትም ረቂቅ የበጀት ማከፋፈያ ቀመር ለብሔረሰቦች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁንም አያይዘው ገልጸዋል።

ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና የመሠረተ-ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ በጀቱ ከፌዴራል መንግስት ድጎማ፣ ከዉጭ እርዳታና ከክልሉ የዉስጥ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን ገልፀዋል።

ረቂቅ በጀቱ አስፈላጊው ዝግጅትና በቂ ምክክር በየደረጃዉ ከሚገኙ የባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጎበት እንዲሁም የተቀመጠዉን የዞኖች የድጎማ ቀመር ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን አቶ ዕንቁ አስታውቀዋል። 

የረቂቅ በጀቱን ዝርዝር መግለጫዎች የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የበጀቱን ከግማሽ በመቶ በላይ በዉስጥ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተፈሪ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ መጠቀምና ዉስን የሆነውን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከበጀቱ 20 በመቶ ለክልል ማዕከል፣ 80 በመቶው ወደታችኛው እርከኖች ላሉ መዋቅሮች የሚዉል መሆኑም ተገልጿል።

Leave a Reply