የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ሀገራዊ ኩነቶች!  

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልሉ ሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ ከተመሠረተ የአንድ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ የክልሉ የአንድ ዓመት ጉዞ ለፈተናዎች ያልተበገረ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ስኬቶች የታጀበ ነው፡፡    

ብዝኅነትና ህብረ-ብሔራዊነት መለያው የሆነው ክልሉ፤ የክልሉን ህዝቦች አብሮ የመልማት የጋራ ህልም ዕውን ማድረግ በሚያስችል አግባብ ተደራጅቶ ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግስት ለክልሉ ህዝቦች የጋራ ህልምና ትልም ስኬት ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ፤ በክልሉ የተረጋጋ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር በሁሉም የልማት አውታሮች አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡   

የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት የሆነው ክልሉ፤ የተለያዩ የልማት ኢንሼቲቮችን ቀርጾ መላው ህዝብን በማስተባበር  የተሳለጠ የምርታማነት ጉዞ ላይ ከመሆኑም ባሻገር፤ በተመሰረተ ባጭር ጊዜ ውሰጥ የተለያዩ ታላላቅ ሀገራዊ ኩነቶችን በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀት አቅሙን ማሳየትም ችሏል፡፡  

ለአብነት፡- በስኬት ከተጠናቀቀው ክልሉ ምስረታ ጀምሮ በተመሰረተ በ6ኛው ወር፤ 9ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በውቢቷ ወላይታ ሶዶ ከተማ እጅግ ታሪካዊ በሚባል ደረጃ በከፍተኛ ድምቀት ማዘጋጀቱ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከታላላቅ ሀገራዊ ኩነቶች አንዱ የሆነው ፎረሙ፤ ከመላው የኢትዮጵያ ከተሞች የመጡ ተሳታፊዎች ለአንድ ሳምንት በዘለቀ ቆይታ የከተሞችን ትስስርና ትብብር ባጠናከሩ የተለያዩ ኩነቶች ተከብሮ በሁሉ ረገድ በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ 

በወቅቱ ወጣቱ፤ የንግዱ ህብረተሰብ፤ መንግስት ሠራተኛውና አጠቃላይ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች፤ ከተማዋን ከማስዋብ ጀምሮ በድንቅ የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴት ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ እንግዶችን ተቀብለው ያማረና የሰመረ ቆይታ እንዲኖራቸው በማድረግ የፎረሙ ድምቀቶች ሆነው አልፈዋል፡፡

ክልሉ ዛሬም በተመሰረተ በአንድ ዓመቱ ሌላ ታላቅ ሀገራዊ ኩነት፡- 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን የማዘጋጀት ሀገራዊ ሃላፊነት ተረክቦ፤ በዓሉን በተለየ ድምቀት ለማዘጋጀት ዝግጁቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ 

የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉ 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ እንዲያዘጋጅ ከአመት በፊት ጅግጅጋ ላይ ሲወስን በምክንያት ነው፡፡

የክልሉ ህዝቦች ላነሱዋቸው በክልል የመደራጀት ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ፤ በሀገራዊ ለውጡ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሕገ-መንግስታዊ ምላሽ ያገኙበት ወቅት መሆኑ ከመነሻ ምክንያቶቹ አንዱና ዋነኛው ነው ሲል ምክር ቤቱ ይገልጻል፡፡ 

ክልሉ በሀገሪቱ ከሚገኙ 76 ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል 32ቱ አንድነታቸውን በጠንካራ የህብረብሔራዊ መሠረት ላይ አፅንተው፤ ለጋራ ህልማቸው ስኬት ተባብረው በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት ቀዳሚው የብዝኅ ህዝቦች ክልል መሆኑ ሌላው ምክንያት መሆኑም ታውቋል፡፡ 

ምክር ቤቱ ክብረ በዓሉ በክልሉ በውቢቷ አርባ ምንጭ ከተማም እንዲከበር ሲወስን፤ የክልሉ ህዝብ ምክር ቤት መቀመጫ መሆኗን እንዲሁም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ምሶሶ በሆነው የቱሪዝም ዘርፍ እንደ ሀገር ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ከግምት በማስገባት ጭምር ነው፡፡

ከክልሉ ማዕከላት አንዷ የሆነችው አርባ ምንጭ፤ በርካታ የቱሪስት መስህብና ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለባት፤ በህብር ህዝቦች ማዕከልነቷ የምትታወቅና በፈጣን የዕድገት ጉዳና ላይ የሚትገኝ ከተማ ነች፡፡

ከዚህ ባለፈ ክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ትኩረት በመሳብ የኮንፍረንስ ማዕከል በመሆን ላይ ሲሆን፤ ሀገራዊ ኩነቶችን ማዘጋጀቱና ማስተናገዱ የክልሉን ኢኮኖሚና ዕድገት በማነቃቃት ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል፤ ከህዳር 25 እስከ 29 በአርባ ምንጭ ከተማ የክልሉን ገፅታ በሚያጎላ አግባብ በልዩ ድምቀት ይከበራል፡፡

በዓሉን ለማክበር ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንግዶች፤ የክልሉ አንዱ ማዕከል በሆነው በወላይታ ሶዶ ከተማ የአንድ ቀን ቆይታ የሚኖራቸው ሲሆን፤ ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ስራው  በስኬት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎችና መላው የክልሉ ህዝቦች ለክብረ በዓሉ በድምቀትና በስኬት መከበር ጉልህ ድርሻ በማበርከት፤ የዚህ ደማቅ ታሪክ አካል መሆን ይገባል፡፡

ሰናይ ሰንበት!

Leave a Reply