ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የመካከለኛ ዘመን የጤና ልማትና ኢንቨስትመን ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 በጀት አመት መነሻ ዕቅድ ዙሪያ ከአስፈጻሚ እና የተለያዩ ባላድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ የቢሮውን የ2016 በጀት አመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም በመገምገም፤ የነበሩ ጥንካሬዎች፤ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በጥልቀት ተወያይቷል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ መንግስት ሰው ተኮር ተግባራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን በማመን፤ በማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ሪፎርሞችን በማድረግ ሊቀመር የሚችል ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል።
የጤና ልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ብዙ ችግር ያለበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሆኖም መንግስት አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረጉ ረገድ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀው፤ ኮቪድን የተሻገርንበት መንገድ ለዚህ እንደ አብነት ሊጠቀስ የሚችል ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የተቸገረን የሚያግዙ መሆን ይኖርባቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በእጅጉ የተሻለ ጤና ተቋም ቢኖርም በአንፃሩ የተበላሹ የጤና ተቋማት መኖራቸው ህብረተሰቡን ለጉዳት በመዳረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
የጤና ተቋማት አደረጃጀትና አሰራር ምን ይመስላል የሚለውን ቆም ብሎ ማየትና መገምገም ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጤና ተቋማት ፅዱ፤ ምቹ፤ ማራኪ እና የተቀላጠፍ ብቁ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የጤና አስተዳድር እና አመራር የጤና ዘርፍ ስራን ለማሳለጥ በእጅጉ የሚረዱ መሆናቸውንም በመግለጽ፤ ኃላፊነት የሚሰማቸው ህይወታቸውን ሰጥተው የሚሰሩ ምስጉን የጤና ባለሞያዎች የመኖራቸውን ያህል፤ የፈፀሙትን ቃለ ማሀላ ወደ ጎን በመተው በገንዘብ እና ቅንነት በጎደለው መንገድ ህብረተሰቡን የሚያገለግሉ በመኖራቸው የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለፈተና መዳረጉን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ምቹ የጤና ተቋማትን በማጠናከርና በማስፋት፤ ጥራት ያለው መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለዜጎች መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አያይዘው በመዳህኒት አቅርቦት ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለማሻሻል የተሻለ የጤና መድህን ስራ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
የእናቶችና ህፃናት ጤና ከመጠበቀ አኳያ በተለይ በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው አከባቢዎች ላይ የተለየ ክትትል የሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ማጠቃለያ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ፤ በተለይ በክልሉ የጤና አገልግሎትን ከማሻሻል አንጻር የተለያዩ ነጥቦችን ያነሱ ሲሆን፤ ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
*አመራሩ የሚመራበትን ስረዓት በየወቅቱ በመገምገም ክፍተቶችን ማረም -አመራሩ የሚመራበት ስረዓት ምን ይመስላል የሚለውን በየጊዜው መገምገም እና ጉደለቶችን በመለየት ማሻሻል ይገባል፤
*የጤና ተቋማትን ማጠናከርና ብቃት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ፡-የጤና ተቋማት ለአገልግሎት ምቹ መሆናቸውን በመለየት፣ ለሰው ልጅ ፈውስ የሚሆኑ የጤና ተቋማትን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም የጤና ተቋማትን ብቃት ባለው የሰው ሀይል ማደራጀት፤ ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን ባለሞያዎችም ለይቶ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በማሰልጠን ማብቃት ይገባል፡፡
*የጤና ተቋማትን በቁሳዊ ግብዓት በማሟላት ህክምናን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማሟላት መስራት ያስፈልጋል፡፡
እንደዚሁም በህክምና ተቋማት ተከማችተው የሚገኙ ግበዓቶችን በአግባቡ በመጠቀም ለህብረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት፤
*በጤናው ዘርፍ የመረጃ ስረዓትን ማሻሻል፡- ዞኖች የተሟላና ታማዓኒ በሆነ መንገድ መረጃ መስጠት እንዲሁም የመረጃ አያያዝ ስረዓታቸውን በማዘመን ወረርሽኞች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል፤
ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2016 በክልሉ ያጋጠመን የወረርሽኝ በሽታ ለመከላከል የተቀናጀ የበሽታ መከላከል ተግባር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት አሳስበዋል።
*ጤናን ከመደገፍና በጤና መስክ የተቀመጡ ግቦችን ከማሳካት አንፃር፡- የጤና ተቋማት እና አስተዳደር ዘርፉ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት፣ በተረዱት መሰረት ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት፣ ችግሩን ለመፍታት መግባባት ላይ መድረስ እና የተግባቡበትን የመፍትሄ ሀሳብ በቁርጠኝነት መፈፀምና ማስፈፀም ይገባል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የዜጎቻችንን ጤና መጠበቅ የሁላችንም ማህበራዊ ኃላፊነት ነው በሚል እልህና ቁጭት፤ ከምንጊዜውም በላይ በሙሉ አቅም ወደ ስራ በመግባት ብቃት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ በመግለፅ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።
በመድረኩ የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው ዞኖች እውቅና ተስጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ወላይታ ዞን 1ኛ፤ ጋሞ ዞን 2ኛ፤ ጌዲኦ ዞን 3ኛ በመሆን ተሸላሚ ሆነዋል።